፠ሶበሰ ኪዳንኪ ምክንያተ ድኂን ኢሀሎ፤ ፈለገ እሳት ወደይን እምአስጠመ ኵሎ፡፡ (ድንግል ሆይ ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የሲኦል እሳት ባሰጠመን ነበር፡፡) እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሲዖልን ካየች በኋላ ስለኃጥአን እጅግ እያዘነች ኖረች ፠ የካቲት ፲፮ ቀንም በጎልጎታ ቦታ ቆማ ወደ ልጇ እንዲህ ብላ ለመነች፡፡
፠ጸሎትና ልመናዬን ስማኝ ቃሌንም አድምጥ እኔ እናትህ አገልጋይህ የምለምንህን ይህ ነው፡፡ ፨ መታሰቢያዬን ለሚያደርጉ፣ ፨ አብያተ ክርስቲያኔን ለሚሠሩ፣ ወይም ፨ ለታረዙ ለሚያለብሱ፣ ለተራቡ ለሚያጠግቡ፣ የተጠማውንም ለሚያጠጡ (በስሜ ለድሆችና ለችግረኞች ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጡ)፣ ፨ የታመመውንም የሚጎበኝ፣ ያዘነውንም የሚያረጋጉ፣ የተከዘውንም ደስ የሚያሰኙ ወይም ፨ ምስጋናዬን ለሚጽፉ፣ ልጆቹንም በስሜ ለሚሰይም፣ ፨ በበዓሌም ቀን በማኅሌት ለሚያመሰግን አቤቱ በዓይን ያልታየውን በጆሮ ያልተሰማውን በጎ ዋጋ ስጣቸው፡፡ ፨ በአማላጅነቴም የሚተማመኑትን ሁሉ ከሲዖል ነፃ አድርጋቸው ከአንተ ጋር የደረሰብኝን ረሃብና ጥማቱን መከራውን ሁሉ አስብ አለችው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዳልሽው ይሁንልሽ የሰጠሁሽን ቃልኪዳን እንዳይታበይ በራሴ በባሕርይ አባቴ በአብ በባሕርይ ሕይወቴ በመንፈስ ቅዱስ ማልኩልሽ ብሎ ቃል ኪዳን ሰጣት።
#ሥርዐተ_ማኅሌት_ዘየካቲት_16፤ #በዓለ_ኪዳነ_ምሕረት፡፡ በሃገራችን በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የኪዳነ ምሕረት በዓል የሚቆመው ቁመት፤ የ3ት ዐበይት አድባራት አብነት ናቸው፡፡
እነዚህም፤
1ኛ) የላይ ቤት፤ የደብረ መድኀኒት ዐቢየ እግዚእ ኪዳነ ምሕረት አብነት
2ኛ) የታች ቤት አብነት፤ የደብረ ኃይል ወደብረ ጥበብ በዓታ አብነት
3ኛ) የደፈጫ ኪዳነ ምሕረት አብነት ናቸው፡፡ ስለዚህ እንደ የደብራችሁ ይትበሃል ትጠቀሙበት ዘንድ ሁሉን አዘጋጅተንላችኋል፡፡ የላይ ቤት ከኾነ ‹‹ዘዐቢየ እግዚእ›› የሚለውን፤ የታች ቤት ከኾነ ‹‹ዘበዓታ›› የሚለውን እንድትጠቀሙ እናሳስባልን፡፡
በፎቶ ላይ ያሉት ቤተክርስቲያን፤
1ኛ) #እንጦጦ_ሐመረ_ኖኅ
_ኪዳነ_ምሕረት ገዳም፡፡ ይህች ገዳም ታሪኳ ከታላቁ ገዳማችን ዋልድባ (ገዳመ ዋሊ) ለ2ኛ ጊዜ መሥፋፋት (መመሥረት ጋር) የተያያዘ ታሪክ ያላት ናት፡፡ ይኸውም የሸዋ አባቶች ወደ ዋልድባ በ485 ዓ.ም. በንጉሥ አልአሜዳ ዘመነ መንግሥት ባቀኑ ጊዜ የተሰባሰቡባት ቦታ ናት፡፡ እነዚህም አበው ከመኖሪያ ቀዬቸው (ቡልጋ/ምንጃር/) ሁለት ታቦታትን (ታቦተ ኪዳነ ምሕረት ዘምሕረት አምባ፤ ታቦተ መድኀኔ ዓለምን ዘአብየ ገዳምን) ይዘው ነበር፤ በዚህች በተቀደች ቦታ ይዘዋት በመጡት ታቦተ ኪዳነ ምሕረት ገዳመ ሐመረ ኖኅን መሥረተዋል፡፡ የመድኀኔዓለም ታቦትን ደግሞ በታላቁ ገዳም በዋልድባ አኑረዋል፡፡ ይህች ሐመረ ኖኅ፤ - በ500 ዓ.ም በአባ ሊባኖስ የአንድነት ገዳም ሆና ተስፋፍታ ተቋቋመች፡፡ - በ9ኛ መቶ ክ/ዘመን ዮዲት ጉዲት የአክሱም ጽዮንን ቤተ መቅደስ ለማቃጠል ስትነሳ ንጉሡ አንበሣ ውድም ታቦተ ጽዮንን በምሥጢር በማስያዝ ወደ ሸዋ መጥተው በእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነምሕረት ገዳም ታቦተ ጽዮንን አሳድረው ወደ ዝዋይ ደሴት ሲሄዱ ለገዳሟ ንዋየ ቅድሰት ስጦታ አበርክተዋል ጸበሏን ተጠምቀው ቦታውን መርቀው ሄደዋል፡፡ - በ12ኛው መቶ ክ/ዘመን ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከንጉሥ ላሊበላ ጋር ወደ ዝቋላ አምባ ሲመጡ በዚህች ገዳም በእንግድነት አድረው በጸበሏ ተጠምቀው ቦታውን ባርከዋል፡፡ - አፄ ዘርዓ ያዕቆብም ወደዚህች ገዳም መጥተው አቀማመጧንና የጸበሏን ፈዋሽነት ተመልክተዋል ‹‹ዳሯ እሳት መሐሏ ገነት ይሁን›› ብለው ብዙ ስጦታ አበርክተዋል፡፡ - አፄ ልብነ ድንግልም ወደ ገዳሟ መጥተው ተማህጽኖ አድርገው በጸበሏ ተጠምቀው ታቦተ ልደታንና ብዙ ንዋየቅድሳት ሰጥተው ሄደዋል፡፡ - በንግሥት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት ይህች ገዳም ሐመረ ኖኅ ኪዳነምህረት ገዳም ተብላ ተሰይማለች፡፡ ይህች ቦታ ከታላቁ ገዳም ከዋልድባ ጋር አሁንም ግንኙነቷ እንደጠነከረ ነው፤ ከዋልድባ ያሉ አባቶች በተለያየ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ በዋነኛነት የሚያርፉባት ጥንተ ርስታቸውም ናት፡፡ ይህች ቦታ በርካት ቅዱሳን በኪደተ እግር የረገጧት እንደመኾኗ፤ ጸበሏ የአጋንንት ድል መንሻ፤ የብዙ መነኮሳት መጠጊያ፤ የህሙማን መፈወሻ፤ የእመቤታችንን ቃል ኪዳን ለማግኘት ብዙን ጊዜ ለሱባኤ ከሚመረጡ ቦታዎችም አንዷ ናት፡፡
2ኛ) #ደብረ_መድኀኒት_ዐቢየ_እግዚእ _ኪዳነ_ምሕረት፤ . በሃገራችን ኢትዮጵያ የመጻሕፍተ ብሉያት አንድምታ ትርጓሜ ዋና ማስመስከሪያ መካነ አእምሮ (University) የኾነች፤ . ታላቁ ጻድቅ አቡነ ዐቢየ እግዚእ በኪደተ እግር የረገጧት፤ . በአቋቋም በኩልም የላይ ቤት አብነት የኾነች፤ . የታላላቅ ሊቃውንት መፍለቂያና ታላላቅ ሊቃወንት ወንበር ዘርግተው፥ ጕባኤ አስፋፍተው ያስተማሩባትና በማስተማር ላይ ያሉባት ቦታ ናት፡፡ የምትገኘውም ጎንደር ከተማ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment